የሜጋ ቸርቾች እና ‹‹የተአምር አድርጊዎች›› ጉዳይ

የሜጋ ቸርቾች እና ‹‹የተአምር አድርጊዎች›› ጉዳይ

By  EYASPED

—————

በመሰረቱ ዝርዝር ጉዳዮችን ትተን የሜጋ ቸርች እና የpersonal prophecy አገልግሎት ከ አዲስ ኪዳን አስተምህሮ ያፈነገጠ አካሄድ ነው፡፡ ክርስትና peak ላይ ሲደርስ ሲሆን ሲሆን ሀዋርያት ስራ ላይ እንደሚታየው ምእመናን ኑሯቸውን በጋራ የሚያደርጉበት ይህ እንኳን ባይሆን በመካከላቸው እጅግ የጠበቀ ቤተሰባዊነት የሚኖርበት ግለሰባዊነት እና ግለሰብን ማዕከል ያደረጉ ትምህርቶች እና ትንቢቶች የሌሉበት ነው፡፡ አሁን እንደሚታየው አይነት በፍፁም በመልክ እንኳን የማይተዋወቁ ሰዎች በትልቅ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው ‹‹በነብዩ›› በስም እየተጠሩ ‹‹እንዲህ እና እንዲያ በግል ህይወትህ ላይ ይሆንልሀል›› በሚሉ ድራማዎች የታጨቀ ነገር በአዲስ ኪዳን ውስጥም በሀዋርያቱ ልምምድ ውስጥ የሚገኝ ነገር አይደለም፡፡ በእንዲህ ያሉ ‹‹አገልግሎቶች›› ላይ ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ይተዩኛል

1ኛ፡- በቅዱሳን መካከል ሊኖር የሚገባውን የጠበቀ የእርስ በእርስ መሰተጋብር የሚያስቀር እና በሳምንት አንድ ቀን በአዳራሽ ውስጥ ተሰብስቦ ‹‹ተአምር አድራጊው›› ተአምር ሲያደርግ አይቶ መበተንን በመንፈሳዊ ህይወት እና ትምህርት እንደማደግ የሚያስቆጥር መሆኑ

2ኛ፡- በእንደዚህ አይነት ሜጋ ቸርቾች ውስጥ በታላቅ ቁጥር በሚደረጉ መሰባሰቦች መካከል ‹‹በተአምር አድራጊው›› የሚነገሩ ትንቢቶች እና የሚሰጡ ትምህርቶች ከመፅሀፍ ቅዱስ ትምህርት የሚቃረኑ እና የግለሰቦችን ስሜት በሚኮረኩሩ መልኩ በግለሰባዊ ብልፅግና እና ስኬት ዙሪያ በማጠንጠን ዋናውን የክርስትና አስተምህሮ እና የክርስቲያኖችን ተስፋ የሚያስረሱ መሆናቸው ነው፡፡

በእነዚህ ሜጋ ቸርች ‹‹የሚያገለግሉ›› ‹‹ተአምር አድራጊዎችም›› በጠባቡ ባልታጠረ የተሰባጠረ እልፍ አእላፍ ምእመናን ዘንድ ማገልገላቸው የትመጤነታቸው (their back ground) እንዳይታወቅ ከማድረጉም በላይ ያለተቆጣጣሪ እንደፈለጉ እንዲባልጉ እድሉን ይሰጣቸዋል፡፡ ለዚህም ነው አብዛኞቹ የሜጋ ቸርች ‹‹ተአምር አድራጊዎች›› ላይ የጀርባ ጥናት ሲደረግ አግብተው የፈቱ፣ ከአንድ በላይ ሚስት ያላቸው፣ ከምዕመናን እንዲሁም ከኳየር አባላት መካከል የተወሰኑትን ያማገጡ፣ባለትዳሮችን ያፋቱ፣ የሰው ገንዘብ የዘረፉ፣ ዘርፈውም ምስጢሩ እንዳይወጣ ያስፈራሩ፣ ምንጩ ግልፅ ያልሆነ ከፍተኛ ሀብት እና ንብረት ያከማቹ ሆነው የሚገኙት፡፡ በእንዲህ ያሉ ‹‹ተአምር አድራጊዎች›› ሰበብ ህይወታቸው የተመሰቃቀለባቸውን ሰዎች ቤቱ ይቁጠረው ከማለት ውጭ ዘርዝሮ ለማስቀመጥ ከቁጥር በላይ ነው፡፡ እነኚህ ተዓምር አድራጊዎች አንዳንዴም በራሳቸው አፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ በካዳሚዎቻቸው አማካኝነት ‹‹እ/ር በቀባው ላይ እጅህን አታንሳ›› ‹‹ማን ፈራጅ አደረገህ›› ‹‹ግለሰቡ የባህሪ ጉድለት ቢኖርበትም ዋናው ቅባቱን ነው ማየት ያለብህ›› ወዘተረፈ በሚሉ መከላከያዎች ጥያቄ የሚያነሱባቸውን ምዕመናን አፍ ለማዘጋት ይሯሯጣሉ፡፡ በአዳራሹ ውስጥ የተሰበሰቡት ምእመናንም እርስ በእርስ የማይተዋወቁ እና ከተለያየ ቦታ የመጡ መሆናቸውም በአንድ ላይ ሆነው ጥያቄ ለማንሳት ስለማያስችላቸው ‹‹ተአምር አድራጊዎቹ›› እንደፈለጉ እንዲፈነጩ አስችሏቸዋል፡፡

ሌላው ዋና ጉዳይ ደግሞ እነዚህ ‹‹ተአምር አድራጊዎች›› በየሳምንቱ የስኬት እና የጥርመሳ ትንቢት ከመናገር ባለፈ መሰረታዊ የክርስትና አስተምህሮ (ስላሴ፣ ደህንነት፣ የክርስቶስ ሞት እና ትንሳኤ፣ ዳግም ምፅአት ወዘተረፈ) ላይ ምንም ሲሉ ስለማይደመጡ በምን አይነት ኑፋቄ ውስጥ እንደተዘፈቁ እና በማን ሀይል ተአምር እንደሚያደርጉ ለመለየት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ቃለ እ/ር ሰይጣንም የብርሀን መልአክ እስኪመስል ድረስ ራሱን ይለውጣል ይላልና በመድረኩ ላይ በሚደረጉ ተአምራቶች እነዚህን ሰዎች እውነተኛ አድርጎ መውሰድ ስህተት ነው፡፡ የወንጌላውያን ባህልን ስለተላበሱ፣ የኢየሱስን ስም ስለጠሩ፣ ጥቅስ ስለጠቀሱ፣ የምናወቀውን መዝሙር ስለዘመሩ፣ ‹‹በማይታወቅ ቋንቋ›› ስለተናገሩ ወዘተረፈ ከእኛ ወገን ናቸው ማለት አይደለም፡፡

እነዚህ ተአምር አድራጊዎች ተአምር ከማድረግ ጊዜ ተርፏቸው አልፎ አልፎ ትምህርት ሲሰጡ ላስተዋለ ምን ያህል ኑፋቄ እንደሚያስተምሩ ለመረዳት ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእኛን ሀገር ጨምሮ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች ‹‹የተነሱ›› ከጎኔ የሚቆም መልአክ አለ…. ቤትህ እንዲህ አይነት ነው፣ ሚስትህ ስሟ እንትና ነው፣ ወንድምህ እንትና ነው ስሙ፣ ትናንት ማታ ከሚስትህ ጋር ስትጨቃጨቁ ነበራችሁ…እኔና መልአኩ በመንፈስ ቤታችሁ ነበርን ወዘተረፈ እያሉ በትክክል የሆነ እና የተከሰተን ነገር ያለምንም ማሻማት የሚናገሩ ‹‹ተንባዮች›› ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሰይጥኗል፣ ክርስቲያን መታመም የለበትም፣ ክርስቲያን ድሀ መሆን የለበትም፣ ሁላችንም ሀብታም ካልሆንን ኢየሱስ ዳግም አይመጣም፣ ንጥቀት እና ዳግም ምፅአት የሚባል ነገር የለም፣ ትንሳኤ ሙታን የለም፣ ወዘተረፈ የሚሉትን የኬነት ሀገንን የኑፋቄ ትምህርት የሚያምኑ እና የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ በዚህ ትምህርታቸውም ታላቁን የህዝበ ክርስቲያኑን ተስፋ የሆነውን ዳግም ምፅአት ከክርስቲያኑ ልብ ውስጥ ለማውጣት ተግተው የሚሰሩ ናቸው፡፡ ‹‹ቅባታቸውም›› ከእ/ር ሳይሆን ይህንኑ ትምህርት ከሰጣቸው ከውሸት አባት ነው፡፡

በመሰረቱ ምግባር እና የፀጋ ስጦታ አንዳንዶች እንደሚሉት እና እንደሚያስተምሩት የተነጣጠሉ አይደሉም፡፡ መፅሀፉ ሀሰተኛ አስተማሪዎችን ከፍሪያቸው ታውቋቸዋላችሁ ነው የሚለው፡፡ ፈትቶ ማግባት፣ ባለትዳርን ማማገጥ፣ ሴሰኝነት፣ ምንዝረኝነት፣ የትዳር አጋርን እና የእጮኛን ልብ መስበር፣ ገንዘብ መዝረፍ፣ ወዘተረፈ ፍሪያቸው የሆኑ ሰዎች በምንም ተዓምር የእ/ር ሰዎች አይደሉም፡፡

የሜጋ ቸርቾች እና “የተአምር አድራጊዎች ጉዳይ”