የቅኔ መጻህፍት

የቅኔ መጻህፍት

ሰሞኑን የትርጉም/ Hermenutics / መጽሀፌን ሳነብ (ስከልስ) እነዚህ ሃሳቦች ትኩረቴን ሳቡት ። ለሌሎች ማካፈል ጠቃሚ መስሎ ስለታየኝ እንዲህ አቅርቤዋለሁ።

ማንም ሰው ሲያስተምር፡ ሲሰብክና ሲተረጉም ስለሚናገረው የቃል ክፍል በቂ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል። የግጥም(የቅኔ) ወይም የንባብ መጻህፍትን በእለት ተእለት ኑሮአችንም ሆነ በአገልግሎታችን በጣም እንጠቀምባቸዋለን። ሰለእነዚህ መጻህፍት ምንነትና አላማ መረዳት አካሄዳችንን ለማቅናት ይጠቅመናል።
                                              ምንጭ የኢትዮጵያ ሙሉወንጌል ስነ መለኮት ኮሌጅ Hermenutics ማኑአል
የቅኔ (የንባብ) መጻህፍት
መጽሐፈ ኢዮብ ፣ መዝሙረ ዳዊት ፣ መጽሐፈ ምሳሌ ፣ መጽሐፈ መክብብ እና መኃልየ መኃልየ ዘሰሎሞን የቅኔ ወይም የጥበብ መጻህፍት በመባል ይታወቃሉ።

መጽሐፈ ኢዮብ
ይህ መጽሀፍ በአራቱ ባልንጀሮች በእግዚአብሔር እና ኢዮብ ማካከል የተከናወነን ክርክር የያዘ መጽሐፍ ነወ፡፡ ትክክለኛ የሆኑና ትክክነኛ ያልሆኑ ምክሮች በወሰጡ አሉ።ይህ መጽሐፍ ከህይወት ችግሮች ጋር በተጋፈጥን ጊዜ የኛን ምላሽ ያንጸባረቃል።አንዳንድ ጊዜ ኢዮብን እንሆናለን ለምን ? እንጠይቃለን። ሌላ ጊዜ እንደ ኢዮብ ወዳጆች ለምን ብለው ለሚጠይቁ ሰዎች አማካሪ አድርገን ራሳችንን እንሾማለን።
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የኢዮብ ጓደኞች መከራ የሃጢአት ውጤት ነው፤ ሰው የሚሰቃየው ኃጢአተኛ ሲሆን ብቻ ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት ይዘው በኢዮብ የመከራ ህመም ላይ ሌላ ህመም ሲጨምሩበት እናያለን። መጽሀፉ እንደዚህ ያለ አስተሳሰብ ትክክል እንዳልሆነ የሚያሰተምር ነው። የመጽሀፉን ትርጉም ለመረዳት የተናጋሪዎቹን ሰዎች ሃሳብ በአንድ የሃሳብ ፍሰት መሰመር ውስጥ አስገብተን አንድ የሃሳብ አንጓ አደርገን በማየት ነው። የእያንዳንዱን ሰው ንግግረ በተናጠል ማየት ጠቃሚ ይሆናል።

መዝሙረ ዳዊት
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምናገኛቸው መዝሙራት ሁል ጊዜ ከእግዚአብሔር ለሰው የተነገሩ የእግዚአብሔረ መልእክቶች ወይም ጠንካራ የስነ መለኮት ትምህርት የሚያስተምሩ አስተምህሮዎች(ዶክትሪኖች)ተደርገው መወሰድ አይኖርባቸውም።ነገር ግን መዝሙራት ከሰው ወደ እግዚአብሄር የተነገሩ ወይም የተዘመሩ የአምልኮ ፣ የውዳሴ ፣የምሰጋና ፣ወይም የጸሎት ዘማሬዎች ናቸው። ስለዚህ እነዚህን መዝሙራት ከእግዚአብሔረ ለእኛ የተነገሩ የእግዚአብሔር ቃሎች አድርገን ከመውሰድ መቆጠብ ይገባናል።

መጽሐፈ ምሳሌ
መጽሐፈ ምሳሌ ክፉ ሰውንና ደግ(በጎ)ሰውን በመጥቀስ በጥበብ መኖርን ከሞኝነት ሕይወት ጋር ያነጻጽራል። ሃላፊነት ያለበት የተሳካ የጽድቅ ሕይወት ለመኖር የሚያስችል መመሪያ ያዘጋጃል። እውነተኛ ጠቢብ ሰው በየእለት ህይወቱ ጥበብን በባህሪው የሚገልጽ መሆኑን ያሳያል። መጽሐፈ ምሳሌን ስናነብና ስንተረጉም የተሰወረ መንፈሳዊ መልእክት ለማግኘት ገለጣዎችን በተሳሳተ መንገድ መውሰድ የለብንም። የህይወት መመሪያ እንጂ በቀጥታ እግዚአብሔር ቃል በቃል የተናገረው ትእዛዝ ወይም የተስፋ ቃል አይደለም።
ምሳሌዎችን ለመተርጎም የሚከተለውን አስተውል፡
• ምሳሌዎች አስፈላጊ የሆነውን መልእክት ሁሉ አካተው አልያዙም
• ምሳሌዎች የየእለት ተግባራዊ የህይወት መመሪያን እንጂ ጠንካራ የስነ መለኮት ትምህርት በቀጥታ ማስተላለፍ አላማቸው አይደለም።
• ምሳሌዎች የጥንቱን አለም አስተሳሰብና ባህል የተላበሱ ስለሆነ መለእክታቸው ግልጽ እንዲሆን ለዘመናችን አቻ ትርጉም ሊገኝላቸው ይገባል።

መጽሐፈ መክብብ
መጽሐፈ መክብብ ከእግዚአብሔር የተለየ ሕይወት በምድር ላይ አላማ የሌለውና ትርጉም የለሽ ወይም ከንቱ መሆኑን የሚገልጥ መጽሐፍ ነው። ይህ ከንቱነት የሰውን ጥረት፣ ድካም፣ እውቀት ፣ስኬት፣ እና ደስታ ወዘተ ያጠቃልላል። (መክ 12,13 ፤ የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና እግዚአብሔርን ፍራ፥ ትእዛዙንም ጠብቅ።)

መኃልይ መኃልይ ዘሰሎሞን
ይህ መጽሀፍ የፍቅር መዝሙር ነው። ይህን መዝሙር በእግዚአብሔርና በእስራኤል ወይም በክርስቶስና በቤተክርስትያን የተደረገ አድርጎ ማቅረብ አግባብነት የለውም። የህ የአንዲት ሴትና የአንድ ወንድ ተፋቃሪዎች ፍቅር መሰረት ያደረገ ነው። ይህ ጾታዊ ፍቅርን የሚያሳይ መዝሙር እንዴት ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ተቆጠረ ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ይህ የሆነበት ምክንያት ጤናማና ትክክለኛ የፍቅር ግንኙነት እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠው ክቡር ስጦታ ስለሆነ ነው። ይህንንም ስጦታ ዛሬም ሰው በትክክለኛ መንገድ እንዲኖርበት የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ያስተምራል። ስለዚህ መጽሀፉን ስናነብም ሆነ ስንተረጉም የተለየ ትርጉም በመፈለግ መድከም የለብንም፣ ትክክልም አይደለም። በአንድ ወንድና ሴት መካከል ያለን የፍቅር ስበት የሚተርክ ነው።